"በሴቶች የብስክሌት ስፖርት ሀገሬን ማስጠራት እፈልጋለሁ  " ታዳጊ ፌቨን ፍቃዱ

Published on May 23, 2025
120 views

"በሴቶች የብስክሌት ስፖርት ሀገሬን ማስጠራት እፈልጋለሁ  " ታዳጊ ፌቨን ፍቃዱ

Dire TOTO l  ግንቦት 13 ፣ 2017ዓም

ገና በአፍላ የእድሜ ክልል ላይ የምትገኝ ወጣት ነች፤ ከልጅነቷ ጀምሮ ከሜዳው ጋር  በብስክሌት ግልቢያ እንደጀመረች  ተነጋግራለች፤ ለአመታት ላቧን አፍስሳ በግሏ እየሰራች በመጨረሻ የድሬ ቶቶ ክለብ አሰልጥኖ ለታላቁ መድረክ ለማብቃት ተመልምላለች ፤ ለአክብሮታዊ ምላሿ በማመስገን እነሆ ...

ሰሞኑን በድሬዳዋ እየተካሄደ ባለው የብስክሌት ስፖርት ውድድር  ከወትሮ በተለየ አንዲት ታዳጊ ሴት የእሷ የዕድሜ እኩዮች ከሆኑት ታዳጊ ወንዶች ጋር በበርቱ ስትፎካከር በስፍራው ታድመው የተመለከቷት እድናቆታቸውን ቸረዋታል፡፡

በ6ኛው መላው ድሬዳዋ ጨዋታዎች የብስክሌት ውድድር ላይ ለነገ ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ተስፋ ያላቸው መሆኑን ያስመሰከሩ ታዳጊ የብስክሌት ስፖርተኞች የታዩበት ውድድር ሲሆን ከእነዚህ መካከልም ታዳጊዋ ፌቨን ፍቃዱ ተጠቃሽ ናት ፡፡

ፌቨን ተወልዳ ያደገችው በድሬዳዋ ከተማ ልዩ ስሙ ደቻቱ ተብሎ በሚጠራ ሠፈር ነው ፤ የፊታችን ግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ.ም 14ኛ ዓመት የልደት በአሏን ለማክበር የተዘጋጀችው ፊቨን ፍቃዱ ፤ በብስክሌት ስፖርት የተሳበችው ገና በልጅነት ዕድሜዋ ላይ ነው፡፡

"አስታውሳለሁ በ9 ዓመቴ አባቴ መሀል ከዚራ ላይ የብስክሌት ውድድር ሲካሄድ ይዞኝ ይሄድ ነበር፡፡ በዛን ወቅት በተለይ በተራ ብስክሌት የሚወዳደሩ ልጆችን አይቼ  ለመጀመሪያ ጊዜ በውስጤ ብስክሌተኛ የመሆን ፍላጎት አደረብኝ " በማለት  ከቶቶ ሚዲያ ኔትወርክ  ጋር በነበራት ቆይታ ተናግራለች፡፡

ገና በልጅነት የተጠነሰሰ የብስክሌት ፍቅር አድጎ ፤ ዛሬ ላይ አብረዋት የሚወዳደሩ ሴት ብስክሌተኞችን ብታጣ ፤ ከእሷ ዕደሜ እኩያ ከሆኑት ታዳጊ ወንድ አማተር  ብስክሌተኞች ጋር በመወዳደር ህልሟ እውን ለማድረግ ጥረቷን ቀጥላለች፡፡

" ምንም እንኳን በአሁኑ ሰዓት እንደ እኔ በብስክሌት ስፖርት በመሳተፍ ላይ ያሉ ሴቶች ባይኖሩም በቅርቡ ግን ጥቂት የማይባሉ ይቀላቀሉኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ " ትላለች፡፡

"ይህቺ ታዳጊ በሴቶች የብስክሌት ውድድር ተሳታፊና ውጤታማ በመሆን የሀገሯ ስም በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ ከፍ ብሎ እንዲጠራ የማድረግ ፍላጎት እንዳላትም ነግራናለች"፡፡

ሴቶች በክለብ ታቅፈው ውድድሮችን በቋሚነት ማካሄድ የሚችሉበትን ሁኔታ እንዲመቻች የምትጠይቀው ፌቨን ፍቃዱ በተለይም በስፖርቱ አካባቢ ያሉት አካላት በጋራ ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል በማለት ተናግራለች፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በቅርቡ የድሬ ቶቶ ክለብ በተለያዩ ዕድሜ ታዳጊዎችን በማሰልጠን ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሳ ሌሎችም የድሬ-ቶቶ ፈለግ በመከተል የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል በማለት መልዕክቷን አስተላልፋለች፡፡

የድሬ ቶቶ ክለብ ታዳጊዎችን ለማሰልጠን ከተመረጡ ሴት ብስክሌተኛ ታዳጊዋ ፌቨን ፍቃዱ አንዷ ነች ፤ ክለቡ ከድሬዳዋ አልፈው ሀገርን በትልልቅ አለም አቀፍ መድረኮች መወከል የሚችሉ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ያለመ እንቅስቃሴ ውስጥ ይገኛል፡፡ የብስክሌት ስፖርት አካዳሚ  እውን ለማድረግ በወንድና በሴቶች የታዳጊ ወጣቶች ምልመላ እያካሄደ ሲሆን በቅርቡም የብስክሌት አካዳሚው የወጣቶች ልማት ኘሮጅክት ኘሮግራም በይፋ ሥራ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡